2009-04-22 15:12:00

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የዕለተ ሮቡዕ አስተምህሮ (እ.አ.አ. ሚያዝያ 22 ቀን 2009)


ቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ ኣሥራ ስድስተኛ ዛሬ ረፋድ በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ አደባባይ በ8ኛ ክፍለ ዘመን ስለ ነበረው ትልቁ የአቡነ ቡሩክ መነኮሳን ኣባል አበምኔት አምብሮዝዮስ ኣውፐርት ጽሑፎች ላይ ያተኮረ ጉባኤ አስተምህሮ አቅርበዋል።

ቅዱሱ አባታችን ጉባኤ አስተምህሮውን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ የሚከተለው ከመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 34 ከቁ 1-9 ተነበበ፤ “እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፥ ምስጋናውንም ዘወትር በአፌ ነው። ነፍሴ በእግዚአብሔር ትከብራለች፥ የተጨቈኑም ሁሉ ይህን ሰምተው ደስ ይላቸዋል። የእግዚአብሔርን ታላቅነት ከእኔ ጋር አስታውቁ፥ በኅብረትም ስሙን እናክብር። እግዚአብሔርን ፈለግሁት መለሰልኝም፥ ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ። ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፥ ፊታችሁም አያፍርም። ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው፥ ከመከራውም ሁሉ አዳነው። የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል። እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው። የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና ቅዱሳኑ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፍሩት።”

ይህ ቃለ እግዚአብሔር በተለያዩ ቋንቋዎች ከተነበበ በኋላ፣ ቅዱስነታቸው በአስተምህሮው መግቢያ ላይ ቤተ ክርስትያን በሰዎች እንደቆመችና በሰዎች እንደምትኖር አመልክተው፣ ቤተ ክርስትያንን ለማወቅ ምሥጢርዋም ለመረዳት፣ መልእክትዋንና ምሥጢርዋን በሕይወት የሚመሰክሩትን ሰዎች ሕይወት ማጥናትና ማወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጠዋል፣ በዕለተ ሮቡዕ በሚያቀርቡት ጉባኤ አስተምህሮ ብዙውን ጊዜ የቤተ ክርስትያን ማንነት ለመማር እንዲረዳ በማለት ስለቤተ ክርስትያን ሰዎች እንደሚያስተምሩም አሳስበዋል። በተለያዩ ጊዜያት ያቀርባቸውን ኣስተምህሮዎች በማስታወስ ከሓዋርያት ጀምረው የቤተክርስትያን አበውንና ሌሎች ትላልቅ ቅዱሳን ሰዎች የተመለከተ አስተምህሮ በማቅረብ ስምንተኛ ክፍለዘመን መድረሳቸውን አብራርተዋል፣ በዚሁ በካርላማኞ ዘመን የሚታወቀው ስምንተኛ ዘመን ብዙ ዕውቅና የሌላቸው እንዲሁም ጽሑፎቻቸው በስሕተት በሌሎች ደራሲዎች ስም የታተመ ትሑት የአቡነ ቡሩክ መነኮሳን አባል አበምኔት አምብሮዝዮስ አውትፐትን አስትውሰዋል።

ይህንን አስመልክተው ቅዱስነታቸው በጣልያነኛ ቋንቋ ሰፊ ኣስተምህሮ ካቀረቡ በኋላ በተለያዩ ቋንቋዎች በአስተዋጽኦ ኣጭር ኣስተምህሮዎችም ሰጥተዋል። በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያቀረቡት እንደሚከተለው ነው።

ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፥ በዛሬው አጠቃላይ አስተምህሮ በ8ኛ ክፍለ ዘመን ስለ ነበረው ትልቁ የአቡነ ቡሩክ መንኮሳን ኣባል አበምኔት አምብሮዝዮስ አውትፐርት ጽሑፎች ለመናገር እወዳለሁ። በመነኮሱ ዘመን የነበረው ችግር የመነኮሳቱን ሕይወት ስለአቃወሰው የአውትፐርት ጽሑፎች መነኮሳቱ የጥሪአቸውን መንፈስ በመቀስቀስ እንዲታደሱ ጥሪ የሚያቀርቡ ናቸው። በብዛት ከሚነንበቡት መጻሕፍቶቹ አንዱ “በሓጢኣትና በመንፈሳውያን ኃይላት መሀከል ያለው ግጭት” የሚል ርእስ የያዘ ሆኖ፣ ዓላማዉም መነኮሳቱን በዕለታዊ መንፈሳዊ ተጋድሎአቸው እንዲረዳቸው ነው። ነፍስን የሚጻረሩ 24 ኃጢኣቶች በመጥቀስ ክርስትያን እያንዳንዱን ኃጢአት የሚቃወምበት መንፈሳዊ ኃይልን በማመልከት ፈተናን የሚያሸንፉበት ዘዴ ያስተምራል። በዘመኑ የነበረውን የሥልጣንና የሃብት ስስት በመታዘብ ስስት የኃጢአት ሁሉ ምንጭ መሆንዋን አስተምሮ የጊዜውን ሰዎች በወንጌል የተመለከተውን ወደ ሕይወት የምትመራ ጠባብዋን ጎዳና እንዲከተሉ ተማጥነዋል።

ሌላው ትልቅ ጽሑፋቸው በራእዩ ለዮሓንስ ላይ ያቀረቡት ጥናት ነው። ይህ ጥናት ስለቤተክርስትያን የቀረበ ጥናትም ነው። አውትፐርት በዚሁ ጽሑፍ “ክርስቶስ የእርሱ ኣካል በሆነው በእኛ ውስጥ በየዕለቱ፣ መወለድ፣ መሞትና፣ መነሣት አለበት” ይላል። ድንግል ማርያም የቤተ ክርስትያን አርአያ ናት። አውትፐርት በምዕራብ እንደ ትልቁ የማርያም ሥነ መለኮታዊ ጸሕፊ ተብሎም ይጠራል፣ ጥልቀት በተሞላበት መንፈሳውነትም ስለ ብፅዕት እመቤታችን ድንግል ማርያም ጽፎአል።

እግዚአብሔርን የማወቅ ቁልፍ ፍቅር ነው ይላል። አእምሮአዊ ጥናት መንገዱን ሊያመለክትልን ይችላል፣ እግዚአብሔርን በእውነት የምናውቀው ግን በፍቅር ነው ይላል። የአውትፐርትን ትምህርት በመከተል ከዕለት ለዕለት በእግዚአብሔር ፍቅር ለማደግ እንሞክር። በማለት የዛሬው ጉባኤ አስተምህሮ ደምድመዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.