2009-04-20 18:10:05

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የንግሥተ ሰማያት ጸሎት ኣስተምህሮ (እ.አ.አ. ሚያዝያ 19 ቀን 2009 ዓ.ም.)


እዚህ ከእኔ ጋር አብራችሁ ለመጸለይ ለተሰበሰባችሁ እንዲሁም በረድዮና በተለቪዥን አማካኝነት ለምትከታተሉ ውድ ውንድሞቼና እኅቶቼ፣ የዘመነ ትንሣኤ አንደኛ ሳምንት ፍጻሜ በሆነው በዛሬዉ እሁድ እንደገና ከልብ የመነጨ መልካም የትንሣኤ ምኞቴን አሳድሳለሁ። በዚሁ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ ክርስቶስ እምነት በሚገኝ የደስታ መንፈስ በሞላበት ወቅት እጎኔ በመቆም በጸሎት ስለረዳችሁኝ፣ በተለይም ባለፈው ሚያዝያ 16 ቀን ላከበርኩት 82ኛ የልደቴ በዓልና ዛሬ ለማስታውሰው ለመንበረ ጴጥሮስ የተሾምኩለት 4ኛ መታሰቢያ ዓመት ለገለጻችሁልኝ መልካም ምኞትና ስላሳረጋችሁት ጸሎት ለሁላችሁም ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እግዚአብሔርንም ስለዚህ ሁሉ አመሰግናለሁ። በቅርቡ እንደገለጽኩትም ለብቻዬ ሆኖ ኣይሰማኝም። በተለይም የትልቁ የትንሣኤ ቀንን ማእከል ባደረገው በዚሁ ሳምንት ከቦኝ ያለ የሚደገፍኝና የሚያጽናናኝ፣ በተለያዩ መንገዶች የተገለጸው ጸሎት ያየለበት መንፈሳዊ ኅብረትና አጋርነትን ማየት ችያለሁ። ይህም ኣብረውኝ ከሚያገለግሉ የሮማ ጉባኤ ወይም ኩርያ ሮማና ጀምሮ እስከ ምድር ዳርቻ ባሉት ቁምስናዎች ስለኔና ለተልእኮዬ የቀረበው ጸሎት ነው። ስለዚህ እኛ ካቶሊካውያን በሓዋርያት ሥራ ምዕራፍ 4 ቁ 32 ላይ፣ “ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ማንም ሰው ይህ የእኔ ነው የሚለው ነገር ኣልነበረውም” ብሎ እንዳረጋገጠው በቀድሞው ክርስትያን ማኅበር መንፈስ ተነቃቅተን አንድ ቤተ ሰብ ያቆምን ነን፣ ይህም ሊሰማን ይገባል።

የመጀመርያው ቤተ ክርስትያን ኣባላት ውህደት እውነተኛ ማእከልና መሠረት ከሞት ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ ነበር። ወንጌል እንደሚነግረን መለኮታዊ መምህር በተያዘበትና ለሞት በተፈረደበት ጊዜ ሓዋርያት ተበትነዋል፣ እመቤታችን ማርያም ጥቂት ሴቶች እና ቅዱስ ዮሓንስ ሓዋርያ ብቻ ከእርሱ አጠገብ ቀርተዉ እስከ ቀራንዮ ድረስ ሸኙት። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለተከታዮቹ ከቀድሞው ይበልጥ ኃያልና የማይበገር አዲስ አንድነት ሰጣቸው። ይህ አንድነት በሰው ልጆች ችሎታና አቅም ሳይሆን ሁሉንም በኢየሱስ እንደተወደዱና ምሕረት እንደተደረገላቸው በሚገልጥ መለኮታዊ ምሕረት ላይ የተመሠረተ ነበር። ስለዚህ ዛሬም እንደትናንቱ ቤተ ክርስትያን አንድ እንድትሆን እንዲሁም አንዲት የሰው ልጆች ቤተ ሰብ የሚያደርጋት የእግዚአብሔር መሐሪ ፍቅር ነው። ይህ መለኮታዊ ፍቅር በተሰቀለውና ከሞት በተነሣው ኢየሱስ አማካኝነት ኃጢአታችንን ይቅር የሚልና መንፈሳችንን የሚያሳድስ ነው። ከእኔ በፊት የነበሩ ዝክረ ጥዑም የእግዚአብሔር አገልጋይ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሓንስ ጳውሎስ 2ኛ በዚህ እምነት ተነሳስተው፣ ይህችን እሁድ ማለትም ከትንሣኤ ቀጥላ የምትውለውን የመለኮታዊ ምሕረት እሁድ ብለው ሰየምዋት። ለዚህም ሁላችን ጌታችን ለቅድስት ፋውስቲና ኮቫልስካ “ኢየሱስ ሆይ ባንተ እተማመናለሁ” በሚል አጭር ጸሎት ያስተላለፈውን መንፈሳዊ መልእክት የመተማመንና የተስፋ ምንጭ የሆነው ከሞት የተነሣ ክርስቶስን እንቀበል።

እንደ የመጀመርያዋ ቤተ ክርስትያን በሕይወታችን ዘመን የምትሸኘን እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት። ንግሥነቷ እንደ የልጅዋ ፍቅርና ምሕረት የበዛበት መሆኑን ስለምናውቅ፣ “ንግሥተ ሰማያት” እያልን እንማጠናታለን። እንደገና ለቤተ ክርስትያን የማቅርበውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለእርሷ አደራነት እንድትሰጡልኝ እጠይቃለሁ፣ በእምነት ኦ እመ ምሕረት ለምኝልን እንበላት።








All the contents on this site are copyrighted ©.