2009-04-19 19:54:40

በዓለ ትንሣኤ

ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ አሥራስድስተኛ በትንሣኤ ቀን ያስተላለፉት መልእክት።


ክርስቶስ ክፋትን ከሥሩ መንቀሉን ኣስታውሰን፣ በሞት ፊት መሸበርንና ተስፋ መቍረጥን እናቁም። የሁሉም ትውልድና ዘመን ሰዎች፣ ክርስቶስ ክፋትን ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል የተጠቀመበትን ትክክለኛ መሣርያ መጠቀም መቻል አለባቸው።

ከሞት በኋላ ምን አለ፧ ይህ ጥያቄ፣ ሰዎች በሕይወታቸው ዘመን በብዛት ከሚጠይቁት ጥያቄዎች አንዱ ነው። ጥያቄው ወይንም ኣንቆቅልሹ መልስ የሚያገኘው፣ በመጨረሻ የሚያሸንፈው ሞት ሳይሆን ሕይወት መሆኑን በሚረጋገጥበት በፋሲካ ወይም በትንሣኤ ነው። የዚህ እርግጠኝነት መሠረት ታሪካዊ እንጂ ተራ በሆነ የሰው ልጅ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ አይደለም።

የተሰቀለውና የተቀበረው ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። ፋሲካ እንዲሁ አንድ ተራ ታሪካዊ ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን አዲስ ሁኔታ የሚጀምርበት ጊዜ ነው። ትንሣኤ ሰው በሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠ ታሪካዊ እውነታ እንጂ ጽንሰ ሓሳባዊ ኣይደለም። ትንሣኤ የዓለማችን በእጅጉ የጨለሙ ቦታዎችና ሥፍራዎች ለማብራት የሚችል ልዩና የማይደገም ታሪካዊ ፍጻሜ ነው። ቁስ አካላዊነትና ባዶነት(nihilism) በሳይንሳዊ ዘዴ ከሚያርጋግጠው አስተሳሰብ አልፎ መሄድ ስለማይችል በቀላሉ ወደ ባዶነትና ኢምንትነት ይወድቃል። የሰው ልጅ ሕይወት የመጨረሻው ዕጣ ፈንታ ወደ ባዶነት እንደሚያደላ ያሰምርበታል። ክርስቶስ ሳይነሳ ቢቀር ኖሮ ባዶነት በነግሠ ነበር። ከሰው ልጅ ሕይወት ክርስቶስና ትንሣኤው ከተወሰዱ ሰው ሊያመልጥ አይችልም ነበር፣ ተስፋው ሁሉ የማይጨበጥ የቁም ቅዥት ሆኖ በቀረ ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ ትንሣኤ ብርሃንና ተስፋ ጥርጣሬው ሁሉ እንዲወገድ ረድቶአል። በክርስቶስ ትንሣኤ፣ ሞት በሰውና በዓለም ላይ የነበረው ኃይልና ሥልጣን ቢያከትምም ቅሉ አንዳንድ የአሮጌው ግዛቱ ምልክቶች ግን ገና ይታያሉ። ክርስቶስ በፋሲካው የክፋት ሥርን ነቅሎ መጣሉ ቢረጋገጥም ቅሉ፣ የየዘመኑ ሰው ሁሉ እርሱ የተጠቀመባቸውን መሣርያዎች ተጠቅመው ድል የእርሱ መሆኑን እንዲረጋገጥ ይተባበሩታል። እኚህ መሣርያዎች የፍትሕ የሐቅ የምሕረትና የይቅርታ እንዲሁም የፍቅር መሣርያዎች ናቸው። በቅርቡ ወደ አፍሪቃ አህጉር ማለት ወደ ካመሩንና አንጎላ ባደረኩት ሓዋርያዊ ጉዞ ያስተላለፍኩት መልእክትም ይህ ነበር።

በእውነቱ አፍሪቃ ልዩ በሆነ ዓይነት ጨካኝና መጨረሻ በሌላቸው ጦርነቶች፣ አብዛኛው ጊዜም በተረሱ ነገር ግን የተለያዩ አገሮችን በሚከፋፍሉና በሚያደሙ እንዲሁም የሚያድጉ ልጆቿ፣ የረሃብ የድህነትና የበሽታ ሰለባ ሆነው እንዲቀሩ በሚያደርጉ ግጭቶች ክፉኛ ትሰቃያለች።

እንዲሁም የጊዜአችን ኣንገብጋቢ ሁኔታዎች፣ በቅድስት መሬት በመካከለኛ ምሥራቅ አገሮችና በመላው ዓለም ተስፋፍቶ ሕዝብን በማሰቃየት ላይ ያለው፣ የምግብ እጦት - የምጣኔ ሃብት ቀውስ - የቆየና አዲሱ ድህነት - የተፈጥሮ አየር ንብረት መዛባት - እና ገዛ አገርን ጥሎ ለመሰደድ ምክንያት የሆነው ችግር ዓለምን ስጋት ውስጥ የከተተው ግበረ ሽበራ እና ሌሎችም ችግሮችም የሚዘነጉ ኣይደሉም። ስለዚህ ሰው ሁሉ በክርስቶስ ትንሣኤ የተጀመረውን ሰላማዊ ፍልምያ እንዳያቋርጥ አደራ እላለሁ።

በመጨረሻም በሃይማኖታቸው ምክንያት ስደትና ስቃይ የሚቀበሉትን የዓለም ክርስትያኖች እናስታውስ፣ እግዚአብሔር ጸጋውንና ኃይሉን እንዲሰጣቸው በተስፋ እንዲበረቱ እንጸልይላቸው።

ቡሩክ ትንሣኤ








All the contents on this site are copyrighted ©.