2009-04-17 12:26:51

ዓርብ ስቅለት


ዛሬ በምሥራቃዊት ቤተ ክርስትያን ሥርዓተ ኣምልኮ ዓርብ ስቅለት ነው። ዓርብ ስቅለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ሕይወቱን የጨረሸበት ቀን ነው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “የሰው ልጅን ይይዙታል፣ ያሥሩታል፣ ይገድሉታል፣ ሆኖም በሦስተኛ ቀን ሊነሣ ነው” በማለት ኣስቀድሞ ነግሮአቸው ነበር።

ጸሓፍትና ፈሪሳውያን ክርስቶስን እንዲገድሉ ተማክረው ነበር። ነገር ግን ሕዝብ ሲያደርገው የነበረውን በማየት ይደግፈው ስለ ነበር፣ በሕዝቡ ዘንድ ግርግር እንዳይነሳና የሚያደርጉትን በበዓል ቀን እንዳይፈጸም ተስማሙ።

እግዚአብሔር የወሰነው ስለማይለወጥ፣ ኣይሁድ ሐሳባቸውን እግብር ላይ ለማዋል የሚረዳቸው ከክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንድ ይሁዳ ኣስቆሮታዊ የተባለውን አገኙ። ክርስቶስ ኣስቀድሞ፣ “መሆን ያለበት መፈጸም ኣይቀረውም ነገር ግን ለዚህ ምክንያት የሚሆን ወዮለት፣ ባይወለድ ይሻለው ነበር” ብሎ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶበት ነበር። አይሁድ ይፈልጉት እንደነበረ፣ ይሁዳ ማንም ሌላ ሳይመለከት ኢየሱስን አሳልፎ ለነሱ ለመስጠት፣ በጨለማ ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቦታ መርቶ ወሰዳቸው። ኢየሱስም እንዳያቸው “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ገመድ ይዛችሁ መጣችሁን፧ በቤተ መቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፣ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው” አላቸው።

አሥረው ወሰዱት፣ ሙሉ ሌሊትን በያይነቱ ስቃይ ሲያወርዱበትና ሲቀልዱበት አደሩ። ከዚህ በኋላ ስለሆነው ቅዱስ ሉቃስ፣ “በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና፣ ኣንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን፧ ኣሉት። እርሱም እኔ እንደሆንሁ እናንተ ትላላችሁ ኣላችው። እነርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ሲል ራሳችን ከአፉ ሰምተናል፣ ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል፧ አሉ” ሲል ይጽፋል።

የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአል በሚል ክስም ወደ ጲላጦስ አቀረቡት። ክሱ እንዲመቻቸውም ለጲላጦስ “እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው” አሉት። ጲላጦስ ከመረመረው ብኋላ “በዚሁ ሰው ላይ ኣንድ በደል እንኳ አላገኘሁም” አላቸው። ከአይሁድ ጋር በገሊላ እንደነበረ ከሰማ በኋላ ጲላጦስ ራሱን ነጻ ለማውጣት፣ ወደ ገሊላ ገዢ ወደ ሄሮድስ ላከው። ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ ብዙ ሰምቶ ስለ ነበረ ከእርሱ አንድ ልዩ ነገርን ለማየት ብዙ ተስፋ አደረገ፣ ሆኖም ክርስቶስ ለጥያቄው እንኳን መልስ ኣልሰጠውም። ከዚህ በኋላ “ሄሮድም ከሠራዊቱ ጋር ናቀው ዘበተበትም፣ የጌጥ ልብስ ኣልብሶም ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው” ይላል ቅዱስ ሉቃስ።

ጲላጦስ በክርስቶስ ላይ ለሞት የሚያበቃ ክስ እንዳላገኘ ደጋግሞ ለአይሁድ ነገራቸው። ነገር ግን ፈሪሳውያንና ጸሓፊዎች ሕዝቡ በክርስቶስ ላይ እንዲነሣ ገፋፉት። ጲላጦስ ሊፈታው እንደሚፈልግ ሦስት ጊዜ ነገራቸው፣ እነርሱ ግን ጩኸት ስላበዙበት፣ “ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም ስለዚህ ቀጥቼ እፈተዋለሁ” ኣላቸው። ስለዚህ ጭፍራዎቹ ከገረፉት በኋላ ልብሱን ገፈው ቀይ ልብስን ኣለበሱት፣ ከእሾህም አክሊል ጐንጒነው በራሱ ላይ ኣኖሩ፣ በቀኝ እጁም መቃ አጨበጡት ወደ ጲላጦስም ወሰዱት፣ እሱም ለሕዝቡ አቀረበው፣ “ይኸውላችሁ እንግዲህ ምን ላድርገው፧” ኣላቸው። እነርሱ ግን “ከእኛ አርቀው፣ ይሰቀል” እያሉ በኃይል ጮሁ።

ጲላጦስ በበዓል ቀን ሕዝብ የፈለገውን አንድ እሥረኛ ይፈታላቸው ነበር። በዚያን ጊዜ በርባን የተባለ አንድ በጣም የታወቀ እሥረኛ በውህኒ ቤት ውሽጥ ይገኝ ነበር፣ ስለዚህ ጲላጦስ “በርባንን ወይስ ኢየሱስ የተባለውን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ፧” ብሎ ሕዝቡን ጠየቀ።

ሕዝቡ ግን በጸሓፍትና በፈሪሳውያን ተገፋፍቶ ባርባንን መረጠ፣ ጲላጦስ ደግሞ ክርስቶስን ምን ላድርገው፧ ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ “ይሰቀል” እያሉ ጩኸትን ኣበዙ። ጲላጦስ በመጨረሻ ሁከት እንዳይነሣ ፈርቶ እንደፈለጉት አደረገላቸው።

ጭፍሮቹ ኢየሱስን ተረከቡ፣ መስቀልም አሸከሙት፣ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክሞ እየወደቀና እየተነሣ ቀራንዮ ወደ ተባለው ስፍራ ደረሰ። ከዚህ በኋላ ጭፍራዎቹ ክርስቶስን በመስቀል ላይ ቸነከሩት፣ መስቀሉን ተከሉት፣ ሕዝቡ ፈሪሳውያንና ጸሓፊዎች “ሊሎችን አድነዋል፣ ለምን ታድያ ራሱን አያድንም፧ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንድናምን ከመስቀሉ ይውረድ፧” እያሉ ይዘብቱበት ነበር። ክርስቶስ ግን “አባቴ ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ይል ነበር። ቅዱስ ሉቃስ ስለክርስቶስ የመጨረሻ ሰዓት ሲናገር፣ “ስድስት ሰዓት ገደማም ነበረ፣ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፣ ፀሓይም ጨለመ፣ የቤተመቅደስ መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። ኢየሱስም በከፍተኛ ድምፅ ጮኸ፣ “ኣባቴ ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ኣለ፣ ይህም ብለ ነፍሱን ሰጠ” ሲል ይጽፋል። የመቶ ዓለቃው የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ” በማለት እግዚአብሔርን አከበረ። ሕዝቡም ሁሉን ከተመለከተ በኋላ በሓዘን ደረቱን እየመታ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ከዚህ በኋላ ዮሴፍ የተባለው የአርማትያስ ሰው፣ ወደ ጲላጦስ ሂዶ የኢየሱስን ሬሳ እንዲሰጠው ለመነ፣ ስለ ፈቀደለትም ከኒቆዲሞስ አብሮ ከመስቀል አወረደው” ሬሳዉን በልብስ ገነዘው፣ ማንም ሌላ ባልተቀበረበት በዓለት የተቆፈረ መቃብር ውስጥም አኖረው።

ሙሉ ቀን የመድኃኒታትን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማትን ስናስተነትንና ስንሰግድ ውለናል፣ ይኽ በእውነት በኢየሱስ ሕማማት ትልቅ ተሳትፎ ነው፣ ሆኖም የድካማችን ትሩፋትን የምናገኝ፣ ሕሊናችንን በምሥጢረ ንስሓ አንጽተን ፋሲካ ሌሊት ሥጋሁና ደሙ ስንቀበል ነው፣ እንዲህ ያደረግን እንደሆነ በእውነት ከክርስቶስ ጋር ተነሥተናል ለማለት እንችላለን።








All the contents on this site are copyrighted ©.