2009-04-15 14:40:39

የዕለተ ረቡዕ ጉባኤ አስተምህሮ


ቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ ኣሥራ ስድስተኛ ለአጭር የዕረፍት ጊዜ ከሚገኙበት የካስተል ጋንደልፎ መንደር የአርእስተ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ሓዋርያዊ ኣደራሽ በሄሊኮፕተር ወደ ቫቲካን ከተማ ተመልሰው፣ ዛሬ ረፋድ በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ አደባባይ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ያተኮረ ጉባኤ አስተምህሮ አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው በጣልያነኛ ቋንቋ ሰፊ ኣስተምህሮ ካቀረቡ በኋላ በተለያዩ ቋንቋዎች በአስተዋጽኦ ኣጭር ኣስተምህሮዎችም ሰጥተዋል። በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያቀረቡት እንደሚከተለው ነው።

ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፥ የዛሬው አጠቃላይ አስተምህሮ በዘመነ ትንሣኤው ሥርዓተ አምልኮ ወቅት መጀመርያ፣ ማለት ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ተደስተን በዓል በምናደርግበት ጊዜ የሚከናወን ነው። የትንሣኤ ዜማዎች የሕይወት ጌታ ከሞት ጋር ታግሎ ካሸነፈ በኋላ ኣሁን በድል በሕይወት እንደሚኖር ያስተጋባል።

ከዓርብ ስቅለቱ የፍኖተ መስቀል ሥርዓት ቀጥሎ የፋሲካ በዓል በማጽናናት በሰላምና በተስፋ የሚታወቀውን የፍኖተ ብርሃን ጊዜ እንድናሳልፍ ያደርገናል። የናዝሬቱ ኢየሱስ ትንሣኤ ታሪካዊነት መመስከርና ማወጅ፦ ለክርስትያናዊ እምነታችን የግድ አስፈላጊነት ያለው ነገር ነው። ክርስቶስ ተነሣ ሲባል፣ ተራ ወደ ሕይወት መመለስን የሚያመለክት አይደለም። ክርስቶስ በትንሣኤው ወደ ኣዲስ ሕይወትና አኗኗር ይገባል። በዚህ ሕይወት ለእያንዳንዱ ሰው ያድሳል። ለመላው ታሪክና ፍጥረትም ይለውጣል።

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች ሲጽፍ፦ “እኔ የተቀበልኩትን በመጀመርያ ደረጃ ያለውን ነገር አስተላልፍሁላችሁ፣ ያስተላለፍሁላችሁም ነገር በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈው ክርስቶስ ሰለኃጢኣታችን ሞተ፣ ተቀበረ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሣ።” ሲል ያሳስባቸዋል። ኢየሱስ የሚሰቃየው የእግዚአብሔር ባርያ በመሆን፣ ኃጢኣታችንን በመሸከምና ስለ እኛ በማማለድ በደላችንን አንድዬ ደምስሶልናል። በሞቱ ሞት እንዲጠፋ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት ደግሞ ወደ ዓለም አዲስ ሕይወት አመጣ።

የጌ.መ.ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ደስታ፣ ወንጌሉን በእምነትና በጽናት ለመኖር እንዲሁም በለጋስነት እንድንመሰክረው ይርዳን።








All the contents on this site are copyrighted ©.